የተስፋ ዘመን – 2021

የወያኔ ጉዳይ ያለቀለት ይመስላል። እነ ደብረጺ “የወንድ በር” ከማፈላለግ ያለፈ አቅም ያላቸው አይመስልም። እንደ አጼ ቴዎድሮስ ሽጉጥ ለመጠጣት አለመዘጋጀታቸው ግልጽ ሆኖአል። እንደሚሰማው ከሆነ ደርዘን የማይሞሉት የወያኔ ቀንደኛ መሪዎች ውስጥ ውስጡን “የወንድ በር” ለማግኘት እየጣሩ ነው። ከተሳካላቸው አሳባቸው ወደ ኢንዶኖዢያ ሄደው ቀሪ ህይወታቸውን ለማሳለፍ ሳይሆን አይቀርም። ዳሩ ረፈደባቸው። በድልድዩ ስር ብዙ ውሃ ካለፈ በሁዋላ መባነናቸው የዘመናችን ምርጥ ስላቅ ሆኖአል።
እንደ ኬርያ ኢብራሂም ወይም እንደ ሴኩቱሬ የመሳሰሉ ደግ እና የዋህ ፖለቲከኞችን ግን ችላ ማለት የሚሻል ይመስለኛል። ብዙ አልጎዱም። ቢለቀቁም ምንም አያደርጉም። እንዲታረሙ ያህል ጥቂት ወራት ቢታሰሩ በርግጥ ጥቂት መጽሃፍት አንብበው ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ዞረም ቀረ መጪው ዘመን እንዲህ ይታየኛል!!
ወያኔ፣ ኮቪድ እና አልሻባብ የሌሉበት አፍሪቃ ቀንድ እየገሰገሰ ሲመጣ ይታየኛል።
ወያኔ በፈጠረው ምስል ምክንያት ተጋሩ ላይ ያረበበው ስሜታዊ ጥላቻ ብን ብሎ ሲጠፋ፣ ብን ብሎ ሲገፈፍ ይታየኛል።
ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ድንበር አልባ አገሮች ሲሆኑ ይታየኛል።
የትግራይ ወጣቶችን የጫኑ አውቶብሶች ዘወትር አርብ ወደ ምጽዋዕ ሲጎርፉ ይታየኛል።
ህዳር ጽዮንን ለማክበር ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን አክሱምን ሲያጨናንቁ ይታዩኛል።
በመላ አፍሪቃ ቀንድ ኦሮምኛ ለመማር ሽሚያ ሲጀመር ይታየኛል።
በመላ አፍሪቃ ቀንድ ስራ በዝቶ፣ ስድብ ጥፍቶ፣ መከባበር ተስፋፍቶ፣ የጦርነት በር ተዘግቶ ጊዜ ወርቅ ሲሆን፣ ፌዝቡክ ጭር ሲል ይታየኛል።
ከአስመራ ከተማ ወደ ሞቅዲሾ የሚጉዋዝ አውቶብስ፣ ከነቀምት ወደ ጎንደር የሚወረወር ባቡር ሲወነጭፍ ይታየኛል።
“በጥንት ዘመን አፍሪቃ ቀንድ የጦርነት ምድር ነበረች” ብሎ የሚጀምር የልጆች የተረት መጽሃፍ በ70 ቁዋንቁዋዎች ታትሞ ሲሰራጭ ይታየኛል።
የአፍሪቃ ቀንድ አገራት በአንድ ገንዘብ ሲገበያዩ፣ አንድ የጋራ ሰራዊት ሲመሰርቱ ይታየኛል።
close

Leave a Reply