የእማሆይ አበራሽ ታሪክ!

ስለ እማሆይ አበራሽ ተሰማ ታሪክ ላውጋችሁ! የተገናኘነው በፈረንጆች የቀን አቆጣጠር በ1999 ነበር።

መጋቢት 5 የአቡየን የንግስ በአል ለማክበር ዝቋላ ሄጄ ስመለስ በአንድ ትልቅ ኦዳ ዛፍ ስር ጠላ፣ ቡና እንዲሁም የእንቁላል ጥብስ በዳቦ ከሚሸጡ ሰዎች ጊዜያዊ ባር እና ካፌ ቁጭ ብዬ ምርጡን የአድአ ጠላ አጣጣምኩ። እኔ ቁጭ ካልኩበት የድንጋይ መቀመጫ እልፍ ብሎ በእድሜ የገፉ እማሆይ ቁጭ ብለዋል።

አብሮኝ የነበረው ሰው በአገጩ ጠቆመኝ፣

“እማሆይ አበራሽ እኒያውልህ!”

ዞር ብዬ አየሁ።
ቆዳቸው የተሸበሸበ፣ ፍም የመሰሉ ደርባባ ሴት ናቸው። የልጅነታቸው ውበት በተጨማደደ ቆዳቸው ላይ ደምቆ ይታያል።

“ማናቸው ባክህ?” ስል ጠየቅሁ።

“አታውቃቸውም?”

“በፍጹም።”

“እማሆይ አበራሽን ሳታውቅ ነው የደብረዘይት ልጅ ነኝ እያልክ ጉራ የምትነዛው?” ብሎ ሳቀ።

“አለማወቅ ሃጢያት አይደለም።” አልኩ።

“በል እንግዲህ ልንገርህ እወቅ። እማሆይ አበራሸ ማለት እኚህ ናቸው። ቢሾፍቱ ተወልደው ደብረዘይት አደጉ። ቢሾፍቱ ላይ አድገው ሲያበቁ ደብረዘይት ላይ መነኮሱ።”

“የተለየ ታሪክ አላቸው?”

“አይ! የላቸውም።”

“ታሪክ ከሌላቸው ታዲያ ስለእሳቸው ማወቅ ምን ያደርግልኛል?”

“በርግጥ ታሪክ ሊባል ባይችልም ኮረዳ ሳሉ ጭናቸው ላይ የእሳት አደጋ ደርሶባቸው ነበር።”

“ምን ማለትህ ነው?”

“አበራሸ በኮረዳነቷ ዘመን ቢሾፍቱ ሃይቅ ዳርቻ ነዋሪ ነበረች። ከእለታት አንድ ቀን ባንድ ምሽት በጣም በረዳት። ብርዱን ለመቀነስ ቀሚሷን ገልባ ምድጃውን አስጠግታ እሳት እየሞቀች ሳለ ከጥጥ የተሰራ ቀሚሷ በእሳት ተያይዞ የግራ እና የቀኝ ጭኗ በእሳት ተጠበሰ። እናም በብዙ ችግር ቁስሉ ዳነላት!”

“እና ይሄ ምን ታሪክ ይባላል?”

“ታሪክ ነው አላልኩም። ምሳሌ ግን ሆኖአል።”

“የምን ምሳሌ?”

“የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም’ የሚባለው ምሳሌ ማለቴ ነው።”

በመደነቅ ስመለከተው ወጉን ቀጠለ፣

“እማሆይ አበራሽን ልታናግራቸው ትችላለህ። የእሳት ቃጠሎውን ታሪክ በዝርዝር ይነግሩሃል። ጠባሳውን ግን አያሳዩህም። ከነፍስ አባታቸው ሌላ ጥቂት ወዳጆቻቸው ጠባሳውን አይተዋል ይባላል። እንደሚባለው ከሆነ የእማሆይ አበራሽን ጠባሳ ያዩ ሁሉ ለዘለአለሙ ፈሪ ሆነው ቀርተዋል!”

እነሆ! የአበራሽን ጠባሳ ባለማየቴ ቆጨኝ።

ለበለጠ መረጃ፥

www.derasii.com

close

1 thought on “የእማሆይ አበራሽ ታሪክ!”

Leave a Reply