የግንቦት ምርጫ!

ኢትዮጵያውያን በመጪው ግንቦት ወር ምርጫ ለማድረግ መወሰናቸውን ሰማሁ። ተገቢነቱ አያጠያይቅም። ጊዜው ግን ያጠያይቃል። “የመፍረስ አደጋ ተደቅኖባታል” እየተባለች የምትታማው ኢትዮጵያ፣ በዘመኑ በሽታ ክፉኛ በመጠቃት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ከ4 ወራት በሁዋላ ምርጫ ለማድረግ መወሰንዋ ስጋት ያጭራል።

(ይህን አስተያየት የሚያነብ “ምናገባህ” ሊለኝ ይችላል። እንኩዋን እኔ ግብጽ እንኩዋ እጅና እግርዋን አስገብታለች። የኢትዮጵያ ጉዳይ መዘዙና ጦሱ፣ ወላፈኑና ጭሱ ከጎረቤት አልፎ ናይጄሪያ እና አልጄሪያ ይደርሳል። ስለዚህ አስተያየቴን ብታነቡ ምንም አይላችሁ።)

“ዴሞክራሲያዊ ቅብጠት” የሚል ቅጽል ስም የሚገባውን የግንቦት ምርጫ የምትሹ እስኪ ሰከን ብላችሁ አስቡ? በቅድሚያ በዚህ ባልተረጋጋ ጊዜ ምርጫ ማድረግ በርግጥ አትራፊ ይሆናል?

መቸም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዴሞክራሲ ፍንጭ የታየው ገና በቅርቡ መሆኑን መካድ አይቻልም። ግብዝ ካልተኮነ በቀር ከነሙሉ ችግሮቹ አብይ አህመድ የመጀመሪያው ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማስፈን ቁርጠኛነት ያሳየ መሪ መሆኑን ማመን ይገባል። ይህ ሰው ቢያንስ የሚሰማ ጆሮ አለው። አይኖቹ ውስጥም ስሜታዊ እንባ አለ። ይህን ሰው ጊዜውን ባልጠበቀ ምርጫ ማወከብ ጉዳቱ አያመዝንም ትላላችሁ?

መቸም የኢትዮጵያ ብዙሃን አጀንዳ “አገሪቱን የሚመራው ማነው?” ከሚለው አጀንዳ በፊት የሚያሳስበው ሰላም እና ምግብ ማግኘት ነው። ስልጣን ላይ ያለው ሰው ኢትዮጵያዊ እስከሆነ ድረስ፣ ታታሪ ስራ ፈጣሪ እስከሆነ ድረስ፣ ሌባ ሞላጫ እስካልሆነ ድረስ፣ አፋኝ ጨቁዋኝ እስካልሆነ ድረስ ተመረጠ አልተመረጠ የሰፊው ህዝብ ቀዳሚ አጀንዳ አይደለም። ህጻን ልጅ በቢላ በሚታረድበት አገር ስለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማውራትም ስላቅ ነው። እንዲያው ለነገሩ “100 % በትግራይ ህዝብ ተመረጠ” ተብሎ የፉገራ ዳንስ የተደነሰለት ደብረጺ የት አለ? ድምጹ ወይም አስከሬኑ እልም ብሎ ሲጠፋ “የት ነህ?” ብሎ የሚጠይቅ ለምን ጠፋ? ምክንያቱ ግልጽ ነው። ምርጫ ቀዳሚ አጀንዳው አይደለም። ከተመረጠው ደብረጺ ያልተመረጠው አብርሃ ደስታ የተጋሩ ወጣቶች ምርጫ ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ አንድ ሰንበት መሰንበት በቂ ነው።

በርግጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ ያስፈልጋል። ጊዜው ካልሆነ ግን ጊዜው እስኪደርስ መጠበቅ የሚገባ ይመስለኛል። ሌሎች አደረጉ ተብሎ አይደረግም። UAE ምርጫ አድርጋ አታውቅም። ዜጎችዋ እንዴት እንደሚኖሩ ግን ይታወቃል። በአንጻሩ እንግሊዞች ምርጫ ካላደረጉ መኖር አይችሉም። ባህላቸው ሆኖአል። በአንድ ወቅት ጋዳፊ እንዲወገድ ምኞት ነበረኝ። የዛሬ ሊቢያን ያየ ግን ጋዳፊን ይናፍቃል። መቸም እንግሊዝን አይታ ኬንያም ምርጫ ታደርጋለች። ተሳክቶላት ግን አያውቅም። “ሲሉ ሰምታ አንዲት የዶሮ ማነቂያ ዶሮ ታንቃ ሞተች” የሚል ጥንታዊ የአማራ ተረት መልእክቱ ግሩም ነው። ምርጫን እያወገዝኩ እንዳይመስል አደራ እላለሁ። “ዴሞክራሲ ባህል ነው። ልምምድ ይፈልጋል።” ማለቴ ነው።

መቸም መከረኛዋ ዙፋን አንድ ናት። ከስር ያሉትን ኩርሲዎች የሚከፋፈሉትም 1000 አይሞሉም። እነዚህን ኩርሲዎች ለጥቂቶች ለማከፋፈል ሲባል ብቻ ሩጫ ምርጫ ሩጫ ዴሞክራሲ አይደለም። ጦስ እንጂ በረከት ሊሆን አይችልም።

እኔ መቸም የአብይ ፖለቲካ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ አይደለሁም። ይህ ሰው የስልጣን ጥም ያለበት ግን አይመስለኝም። አስረክቦ ለመሄድ አይኑን የሚያሽ አይመስለኝም።

እናም ጎረቤቶቼ ሆይ!

አብይን ቁጭ አድርጋችሁ ሌባ ጣታችሁን እያወዛወዛችሁ እንዲህ በሉት፣

“ስማ ሰውዬው! ያለምርጫ 5 አመታት አገራችንን እንድትመራ ፈቅደናል። ይችን እንደ ጠንቁዋይ ተረት የተቀባዠረች አገር እስከ 2018 አስተካክለህ አስረክበን!”

close

Leave a Reply